ኩባንያችን ከተቋቋመበት ከ1886 ዓ.ም ጀምሮ ማሕበረሰባችንን ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር በማስተዋወቅ ኃላፊነቱን ሲወጣ የኖረ የሕዝብ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፤ በአሁኑ ወቅትም የዘመናችንን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና የዲጂታል ሶሉሽኖች በፍጥነት እያቀረበ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይን ቁርጠኝነት ዕውን እያደረገና የማህበረሰባችን የዕለት ከዕለት የአኗኗር ዘይቤን እና የቢዝነስ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም የዚሁ ጥረት አካል የሆነውንና ከዚህ በፊት በቅድመ-ገበያ ሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባና በአዳማ ከተሞች አስጀምሮት የነበረውን የ5ጂ የሞባይል አገልግሎት በአዲሰ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ በ145 ሳይቶች ማስጀመሩን በታላቅ ደስታ ይገልጻል፡፡
ይህ የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት እስከ 10 ጊ.ባ በሰከንድ (Gbs) የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው፣ ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን እጅግ በላቀ ሁኔታ በመቀነስ (Ultra low latency) ወደ 1ሚሊ ሰከንድ የሚያደርስ ሲሆን፣ በተጨማሪም በአንድ ካሬ ኪሎሜትር ውስጥ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ በርካታ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እርስ በርሳቸው ለማገናኘት የሚያስችል ዓለማችን የደረሰበት የመጨረሻ የገመድ አልባ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
5ጂ አገልግሎት በተለይም ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸው (Mission Critical) እና በተመሳሳይ ወቅት መከናወን የሚፈልጉ አገልግሎቶችን (real time) ለአብነትም የማምረቻ ፋብሪካዎች፣ ግብርና፣ ህክምና፣ ለመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች እጅግ የላቀ ፋይዳ ያለው ሲሆን እንደ አሽከርካሪ-አልባ ተሽከርካሪዎች (self-driving vehicles) ፣ Internet of Things የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች በተግባር እውን እንዲሆኑ የሚያስችል አስተማማኝና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
የኩባንያችን 5ጂ አገልግሎት ስራ ላይ መዋል የማሕበረሰባችንን ሕይወት የሚያቀሉ ዲጂታል ሶሉሽኖችን በቀላሉ በማቅረብ ተሞክሮአቸውን የሚያሻሻል ሲሆን ለቢዝነስ ደንበኞቻችን ደግሞ ምርታማነታቸውን እና የአሠራር ቅልጥፍናቸውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ፣ በዘመናዊ መተግበሪያዎች አማካኝነት አዳዲስ ገቢዎችን የሚያስገኝላቸው፣ የቢዝነስ ትንታኔን በቀላሉ በማግኘት ከንግድ ለውጦች ጋር በፍጥነት እንዲላመዱ የሚያግዛቸው እንዲሁም ተለዋዋጭ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ለተልዕኮ-ወሳኝ የሆነ ፈጣን የዳታ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል።በተጨማሪም የ5ጂ የሞባይል አገልግሎት ለዘመናዊ ቤት (Smart home) ፣ ለስማርት የጤና አገልግሎት እና የሆስፒታል አስተዳደር፣ ለስማርት ግብርና፣ ትምህርት፣ ኢንደስትሪ/ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ለስማርት ኤርፖርትና የጉዞ አገልግሎት፣ ለስማርት ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ፣ ለዲጂታል ግብይት (digital shopping) ለማከናወን፣ ለብሮድካስቲንግና ለመዝናኛ እንዲሁም በክላውድ ላይ ለተመሰረተ 5ጂ ጌሞችን ለመጫወት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የዘመናችን የመጨረሻው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ኩባንያችን የ5ጂ አገልግሎትን በአዲሰ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ በ145 ሳይቶች አገልግሎቱን በማስጀመር ለክቡራን ደንበኞቹ ያልተገደበ ዳታ፣ የመደበኛ የመኖሪያ ቤት እንዲሁም የተለያዩ ጥቅሎችን ያቀረበ ሲሆን፣ ደንበኞች እነዚህን አገልግሎቶች ለማግኘት የ5ጂ ሞባይልን ለመጠቀም የሚያስችሉ መሳሪያዎችና ቀፎዎች ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም
ጳጉሜ 4 ቀን 2015 ዓ.ም