ኩባንያችን የኔትወርክ ሽፋን ተደራሽ ባልነበረባቸው ገጠራማ የሀገራችን አካባቢዎች 100 የሞባይል ኔትወርክ ሶሉሽኖች (Rural Mobile Solutions) በመገንባት በ305 የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች የሚኖሩ ከ903 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችን ለመጀመሪያ የጊዜ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ሲያበስር በታላቅ ደስታ ነው!
በአፍሪካ የቴሌኮም አገልግሎትን በማቅረብ ፈር ቀዳጅ የሆነው እና ላለፉት 130 ዓመታት ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለማሕበረሰባችን በሰፊው ተደራሽ በማድረግ በሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ላይ የአስቻይነት ሚናውን በጉልህ እየተወጣ የሚገኘው ኩባንያችን የኔትዎርክ ሽፋን ክፍተት ለመቀነስ የሚያስችለውን አዲስና ዘመናዊ የገጠር ሞባይል ኮኔክቲቪቲ ሶሉሽን በገጠር ቀበሌዎች በመገንባት የገጠሩን ማህበረሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻሉ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ላይ የሚገኘው ኩባንያችን የዲጂታል አካታችነት ክፍተትን ለማጥበብ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገትን ለመደገፍ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም ይፋ ባደረገው መሠረት 500 የገጠር የሞባይል ሶሉሽኖችን በሃገራችን ራቅ ባሉ የገጠር መንደሮች ለመገንባት እቅድ በመያዝ በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ100 የገጠር ሞባይል ኔትወርክ ሶሉሽኖችን እ.ኤ.አ በ2024 ገንብቶ አገልግሎቱን ተደራሽ እንደሚያደርግ ማስታወቁ ይታወሳል።
በዚሁ መሠረት የኔትወርክ ሽፋን ተደራሽ ባልነበረባቸው ገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች 100 የሞባይል ኔትወርክ ሶሉሽኖችን ግንባታ አጠናቆ በ305 የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች ለሚኖሩ ከ903 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የማህበረሰብ አባላት የሞባይል ኮኔክቲቪቲ አገልግሎትን አስጀምሯል፡፡ ይህም ኩባንያችን የትኛውም የማህበረሰብ ክፍል ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት እንዳይገለል ለማድረግ ያስቀመጠውን ቁርጠኛ አቋም የሚያረጋግጥ ነው።
በዛሬውም ዕለት የፕሮጀክቱን የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቅ ተከትሎ የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ ማኔጅመንት ከመስተዳድር አካላት እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በጋራ በመሆን አገልግሎቱ በተጀመረባቸው አካባቢዎች ላይ በአካል በመገኘት የአገልግሎቱን መጀመር በይፋ ለህዝባችን በማብሰር ላይ ይገኛሉ፡፡
ይህ ፕሮጀክት፣ ኩባንያችን፣ የሞባይል ሶሉሽኖችን ራቅ ባሉ የገጠር አካባቢዎች ላይ ለመገንባት የሚገጥሙ እንደመሬት አቀማመጥ፣ የመንገዶች ያለመኖር ፣ የተበታተኑ ሰፈራዎች እና የኃይል አቅርቦት እጥረት ያሉ ተግዳሮቶች ሳይበግሩትና በአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ ወደ ሳይቶቹ በማጓጓዝ የተከላ ስራውን በአጭር ጊዜ አጠናቆ የተገበረው ፕሮጀክት ሲሆን ይህ የገጠር ሞባይል አገልግሎት ሶሉሽን (Rural connectivity solution) በቀላሉ የኔትወርክ አቅም በማሳደግ የ2G፣ የ3G እንዲሁም እንደአስፈላጊነቱ በማዘመን የ4G አገልግሎትን መስጠት የሚያስችል፣ በሶላር ኃይል የሚሰራ፣ የአካባቢ ብክለት የማያስከትል ዘመናዊ ገጽታ የተላበሰ ሶሉሽን ነው።
ይህ የገጠር ኮኔክቲቪቲ አገልግሎት እውን መሆን ኩባንያችንን በአፍሪካ ደረጃ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ካደረጉ ጥቂት ግንባር ቀደም የቴሌኮም ኦፕሬተሮች አንዱ የሚያደርገው ሲሆን ዜጎች የኮኔክቲቪቲ እና ተዛማጅ አገልግሎት ለማግኘት በአማካይ እስከ 20 ኪ.ሜ ያደርጉት የነበረውን ጉዞ በእጅጉ በማሳጠር የገጠራማ አካባቢ ማህበረሰቦቻችን አካታች የዲጂታል እና ፋይናንስ አገልግሎት፣ ዘላቂ ልማት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ይሆናል።
ይህ አገልግሎት በገጠራማ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖረው የማህበረሰብ ክፍል መሰረታዊ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኝ ከማስቻሉም በተጨማሪ በሕዝቦች መካከል የሚኖረውን ኢፍትሀዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስብጥር (Digital Divide) በማጥበብ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በሌሎችም ዘርፎች የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ ለዜጎች ኢኮኖሚያዊ እድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም የዜጎች ህይወት በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የዚህ መሰረተ ልማት መስፋፋት ኩባንያችን አካታችነትን መርህ በማድረግ ተግባራዊ ያደረገው የሞባይል መኒ አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው እጅግ ገጠራማ አካባቢዎች በተበታተነ የአሰፋፈር ሁኔታ የሚኖረው ማህበረሰብ በቴሌብር አማካኝነት ገንዘብ ከመላክ፣ ከመቀበልና ግብይት ከማከናወን ባሻገር ልዩ ልዩ የአነስተኛ ብድር እና ቁጠባ አማራጮችን በመጠቀም ኑሮውን እንዲያሻሽል ብሎም የዲጂታሉን አለም እንዲቀላቀል ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
በቀጣይ ምዕራፍ ኩባንያችን አስፈላጊ ጥናቶችን በማድረግ መሰረታዊ የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው የሀገራችን የገጠር አካባቢዎች የሞባይል አገልግሎቶችን ለማስፋፋት እንዲሁም የገጠር ማህበረሰቦችን የዲጂታል ተካታችነትን ለማምጣት ፣ የኔትወርክ ሽፋን ክፍተቶችን ለማጥበብ እና የገጠሩን ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያረጋግጡ የዲጂታል ሶሉሽኖችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ ተቆጣጣሪ ተቋማት፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የልማት አጋሮች፣የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ተባብረው የበኩላቸውን ድጋፍ እና ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ በተጨማሪም የአካባቢው ማህበረሰብ የኔትወርክ መሰረተ ልማቶችን እንደራሱ በመጠበቅና አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት እንደሚገባ በአጽንኦት ያሳስባል።
በመጨረሻም ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የኩባንያችን ቤተሰቦች፣ ባለድርሻ አካላት እና የአካባቢው ማህበረሰብ ኩባንያችን ከፍ ያለ ምስጋናውን እያቀረበ፣ ለሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታና ለመላው ማህበረሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥ በቴክኖሎጂው ዘርፍ እያከናወናቸው የሚገኙ መጠነሰፊ ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
የገጠር ሞባይል ጣቢያዎች የሚገኙባቸው ቦታዎች
ኢትዮ ቴሌኮም
ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም