ኢትዮ ቴሌኮም ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር የተቋማትን የዕለት ተዕለት የቢዝነስ እንቅስቃሴን ለማዘመን እና ለማሳለጥ እንዲሁም መሪ የዲጂታል አገልግሎት አቅራቢ በመሆን ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የዚህ ጠንካራ ተነሳሽነት እና ራዕይ አካል የሆነ እና ስማርት የሞባይል ስልኮችን በአጋርነት ለማቅረብ እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የሦስትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት ከቴክኖ ሞባይል ኩባንያ እና ትራንሲዮን ማኑፋክቸሪንግ ኃ. የተ.የግ. ኩባንያ ጋር ተፈራርሟል፡፡

የስትራቴጂያዊ አጋርነት ስምምነቱ በዋናነት የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ጥራት ያላቸው የቴክኖ ሞባይል ስልኮችን በሀገር ውስጥ ለመገጣጠምና ለማቅረብ፣ በቂ የሞባይል ስልኮችን እና መለዋወጫዎች (accessories) አቅርቦትን ለማረጋገጥ፣ ደንበኞች የላቀ የዲጂታል ዕውቀት እና ተሞክሮ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ የሞባይል ስልኮችን ለማቅረብ፣ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን እና ይዘቶችን የሚደግፉ ሞባይሎችን ተደራሽ ለማድረግ፣ የአገልግሎ መስጫ ማዕከላትን በጋራ ለመጠቀም፣ የድህረ ሽያጭ አገልግሎትን ለማሻሻል እንዲሁም ስልጠናዎችን እና የቴክኒክ ድጋፎችን በጋራ ለማከናወን የሚያስችሉ ማዕቀፎችን የሚያካትት ነው፡፡

የትብብር ስምምነቱ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የስማርት ሞባይል ስልኮችን ተደራሽነት ለመጨመር፣ ደንበኞች የ4ጂና 5ጂ ኔትዎርክ እንዲሁም የዲጂታል አገልግሎቶችን በስፋት እንዲጠቀሙ ለማስቻል እና በሀገራችን ያለውን ከፍተኛ የዲጂታል አጠቃቀም ክፍተት ለማጥበብ ትልቅ ፋይዳ የሚኖረው ይሆናል፡፡

በተጨማሪም በዛሬው ዕለት ሦስቱ ኩባንያዎች የቴክኖ ሞባይል ኩባንያ ምርት የሆኑትን ካሞን 20 ፕሮ 5ጂ እና ካሞን 20 ፕሪምየም 5ጂ የተሰኙ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተራቀቁ፣ እጅግ ከፍተኛ የካሜራ ጥራትና የፕሮሰሰር አቅም ያላቸው፣ ለረጅም ጊዜ መቆየት የሚችል ባትሪ፣ ማራኪ ቅርጽ እና ውበት ያላቸው የመጨረሻው የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑትን እንዲሁም ደንበኞች የላቀ የአገልግሎት ተሞክሮን እንዲኖራቸው የሚያስችሉ የስማርት ሞባይል ስልኮችን ለግብይት ማቅረባቸውን በጋራ አብስረዋል፡፡

ኩባንያችን እነዚህን ካሞን 20 ፕሮ 5ጂ እና ካሞን 20 ፕሪምየም 5ጂ የተሰኙ ሁለት የስማርት ስልክ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ቸርችል ጎዳና አካባቢ ወይም ሊሴ ገ/ማሪያም ትምህርት ቤት አጠገብ በሚገኘው የደንበኞች ፕሪምየም ቢዝነስ ማዕከል ከ24 ወራት ዋስትና ጋር ለገበያ ያቀረበ ሲሆን፣ የሞባይል ስልኮቹ ለሶስት ተከታታይ ወራት በየወሩ ከነጻ የ100 ጊ.ባ ዳታ ጋር እንዲሁም ከነጻ የሞባይል ሽፋን (phone cover) እና ከገመድ አልባ የጆሮ ማዳመጫ (earbuds) ጋር ቀርበዋል፡፡

በቀጣይም ኩባንያችን እነዚህን እና መሰል ለማህበረሰባችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ፋይዳ ያላቸውን ምርት እና አገልግሎቶችን በሰፊው በማቅረብ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን እና አካታችነትን ለማረጋገጥ በትኩረት የሚሰራ ይሆናል፡፡

                                           ሰኔ 16 ቀን 2015 .

                                                ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives