ይህ ዓመታዊ ዕቅድ የስትራቴጂ ዘመኑ ሁለተኛ ዓመት ሲሆን ከሐምሌ 2015 እስከ ሰኔ 2016 ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው፡፡

ኩባንያችን ላለፉት 129 ዓመታት የቴሌኮም አገልግሎት በመስጠት በሃገራችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም በዜጎች ኑሮ መሻሻል ላይ የበኩሉን አስተዋጽዖ በማድረግ አጠቃላይ የአስቻይነት ሚናውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ በቴሌኮም ውድድር ገበያ ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲሁም ከኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባሻገር የድርጅት እና የግለሰብ ደንበኞችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማሳለጥና አካታች እድገት እንዲኖር የዲጂታል እና የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ ቀዳሚ የመሪነት ሚና ለመጫወት የሚያስችል የሦስት ዓመት ስትራቴጂ ቀርጾ በመተግበር የመጀመሪያውን አንድ ዓመት የላቀ ውጤት በማስመዝገብ አጠናቋል፡፡

የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ የውድድር ገበያውን ታሳቢ ያደረገና ኩባንያችን የደረሰበትን ደረጃ እና የኢንደስትሪውን ለውጥ በማገናዘብ ካለፈው ዓመት ስትራቴጂ አፈጻጸም ግብዓት በመውሰድ፣ የተለያዩ ዳሰሳዎችን በማከናወን በውድድር ገበያው በሁሉም መስክ መሪነቱን በማስቀጠል የሀገራችን የቴሌኮም ዘርፍ የማህበረሰባችን ሁለንተናዊ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዲኖረው ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

የበጀት ዓመቱ እቅድ ሲዘጋጅ የሦስት ዓመቱ ሊድ የዕድገት ስትራቴጂ የመጀመሪያው አንድ ዓመት ትግበራን እና የኩባንያችንን ተወዳዳሪነት እንዲሁም  አስተማማኝ እድገት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተቋሙ ላይ ፍላጎትና ተጽዕኖ ሊኖራቸው የሚችሉ የመንግስት የፖሊሲ ሰነዶችን፣ የመንግስት የልማትና እድገት እቅዶችን (የ10 ዓመት የመንግስት እቅድ እንዲሁም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ እድገት እቅድ)፣ የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላት ፍላጎትና ተጽዕኖን (የደንበኞች፣ የሠራተኞች፣ የተቆጣጣሪ አካላት፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎችና የተለያዩ የመንግስት አካላት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት) ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም በቴሌኮም ዘርፍ የተሰማሩ ሌሎች ተቋማት ያላቸውን የገበያ እንቅስቃሴና ልምድ፣ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ እድገት ዋና ዋና አዝማሚያዎችና የዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመተንተን፣ የተወዳዳሪዎቻችን አካሄድ እንዲሁም የኩባንያችን ውስጣዊ ጥንካሬና ውስንነቶችን በመለየት፣ ውጫዊ መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶችን በመተንተን፣ የተቋሙን ተጨባጭ አቅምን በመለየት ለተወዳዳሪነት የሚያበቃውን ተግባራት በመቃኘት የተዘጋጀ እቅድ ነው፡፡

ዘርፈ ብዙ ምልከታዎችና ከባቢያዊ ሁኔታዎች ትንተና ከተከናወነ በኋላ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን በመለየት እና በስድስቱ ስትራቴጂያዊ የትኩረት መስኮች እንደገና በመፈተሽ ወቅታዊ መሆናቸውን፣ እንዲሁም በዳሰሳዎችና በትንተና የተለዩ መልካም እድሎችን ለመጠቀምና ፈተናዎችን ለመሻገር በሚያስችል መልኩ ተቀርጸዋል፡፡ ይህ ስትራቴጂ የቴሌኮም ዘርፍ በፍጥነት የሚያድግ እና ተለዋዋጭ በመሆኑ ከወቅቱ ጋር በፍጥነት የሚራመድ ተቋም የመሆን ትልም በመንደፍ ዕቅዱ ቋሚ (Static) ሳይሆን በየወቅቱ በኢንዱስትሪው ላይ የሚታዩ እድገትና ለውጦች፣ የመንግስት የእድገት እቅድና አቅጣጫዎች እንዲሁም ከውድድርና ከቀጣይ ሪፎርም ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንና የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ ‘deliberate’ እና ‘emergent strategy approach’ በመከተል የተዘጋጀ ሲሆን ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮች ሲለወጡ እንደ አስፈላጊነቱ ተለዋጭ ሁኔታዎችን መሠረት ባደረገ መልኩ የሚሻሻል ይሆናል፡፡

ራዕይ/Vision

መሪ የዲጂታል መፍትሔዎች አቅራቢ

A Leading Digital Solutions Provider

ተልዕኮ/ Mission

አስተማማኝ የኮሙኒኬሽን እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በማቅረብ ሕይወትን ማቅለል እና የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማፋጠን

Provide Reliable Communications & Digital Financial Services to Simplify Life and Accelerate Digital Transformation of Ethiopia.

እሴት/ Values

  • ሰው ተኮር/ Human- Centric
  • ታማኝነት/ Integrity
  • ልህቀት/ Excellence
  • ማህበራዊ ኃላፊነት/ Socially Responsible
  • አብሮነት/ Togetherness

በስትራቴጂያዊ የትኩረት መስኮች ማለትም ምርጥ የደንበኛ ተሞክሮን ማረጋገጥ፣ ቀጣይነት ያለው የቢዝነስ እድገት፣ የቴክኖሎጂ ልህቀት ማረጋገጥ፣ ሰው ተኮርና ከፍተኛ አፈጻጸም ያለው ተቋም መገንባት፣ የኦፕሬሽን ልህቀት እና ቀዳሚ ተቋማዊ ገጽታ ግንባታ ሥራዎች ኩባንያው ዕውን ለማድረግ ያለውን የሰው ኃይል፣ እውቀትና ሀብት በአግባቡ በመምራት በደንበኞቹ፣ በአጋሮቹና በባለድርሻ አካላት ተመራጭ ኩባንያ ለመሆን የሚንቀሳቀስ ይሆናል፡፡

ስትራቴጂው ስድስት የትኩረት መስኮችን በ17 ስትራቴጂካዊ ግቦችና በርካታ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን (Strategic Initiatives) በመቅረጽ የኩባንያውን ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ እና ትኩረት ለሚሹ ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት (to address strategic issues) ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን የኮርፖሬት ስትራቴጂካዊ ግቦች ተገቢውን መለኪያና ዒላማ ተዘጋጅቶላቸው ወደ የሥራ ክፍሎች ካስኬድ (cascade) በማድረግ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

ስትራቴጂው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የደንበኛ ፍላጎትን ለማርካት፣ የቴሌኮም ስርጸትን በማሳደግ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመደገፍና አጠቃላይ የሀገሪቱን ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የተቋሙን የገቢ ምንጭ ከተለመደው መሠረታዊ የቴሌኮም አገልግሎቶች ወደ ዳታና የይዘት አገልግሎቶች፣ የክላውድ፣ የኢንፍራስትራክቸር እና የኢንተርፕራይዝ ሶልዩሽንስ ትኩረት በማድረግ፣ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ላይ አዳዲስ አገልግሎቶችን በመጨመር እና በማስጀመር በሁሉም ዘርፍ ዝግጅት በማድረግና ያሉትን መልካም ተሞክሮዎች በማጠናከር የተቋሙን ቀጣይነት ያለው እድገትና ትርፋማነትን ለማሳደግና አስተማማኝ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

የኩባንያችን ዋና ዋና እቅዶች

በ2016 በጀት ዓመት የደንበኛ እርካታን የሚያሳድጉና ተሞክሮን የሚያሻሽሉ ጥራት ያላቸው አገልግሎቶች ለማቅረብ ሁለገብ ጥረቶች የሚከናወኑ ሲሆን በተለይም የኩባንያውን እድገት፣ ተወዳዳሪነትና የገበያ ድርሻ ለማስጠበቅ የሚያስችሉ እንዲሁም በዘላቂነት ጠቃሚ (future proof) የሆኑ የኔትወርክና የሲስተም አቅም ማሳደጊያና ማሻሻያ ፕሮጀክቶች እና አዳዲስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የሚተገበሩ ይሆናል፡፡

  • የቴሌኮም ኔትዎርክ ማስፋፋፊያ እና የአገልግሎት ጥራት ማስጠበቂያ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል በተለይም እያደገ የመጣውን የዳታ ተጠቃሚዎች ፍላጎት ለማርካት የ4ጂ/ አድቫንስድ 4ጂ፣ 3ጂ ኔትወርክ ማስፋፋት እና ማትባት፤ የ5ጂ ኔትወርክ ማስፋፊያ በማከናወን አጠቃላይ የሞባይል ኔትወርክ ደንበኛ የማስተናገድ አቅምን 92 ሚሊዮን ማድረስ፤
  • አዳዲስ እና ዘመናዊ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን እና ሲስተሞችን ማስፋፊያና ማጠናከሪያ ፕሮጀክቶችን መተግበር (ዳታ ሴንተር፣ ክላውድ፣ ቢዝነስና ኦፕሬሽን ሳፖርት ሲስተም…)
  • የደንበኞችን ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ ጥራት ያላቸው እና ዋጋቸው ተመጣጣኝ የሆኑ ምርትና አገልግሎቶችን ማቅረብ፣
  • አዳዲስ የገቢ ምንጮችን ማበራከት፣
  • የኢንተርፕራይዝ ደንበኞችን ፍላጎት የሚመልሱ አገልግሎቶችን ማቅረብ፤
  • ለኢንተርፕራይዝ ደንበኞች የሴኩሪቲ ሶልዩሽንስ ማቅረብ፤
  • የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን በተለይም ዲጂታል የአገልግሎት መስጫ አማራጮችን ማብዛት እና የደንበኞች የአገልግሎት ፍላጎት በአፋጣኝ መመለስ፤
  • የተጀመረውን የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን በማጠናከር እንደ አነስተኛ ቁጠባ እና ብድር ያሉ ተጨማሪ የቴሌብር የአገልግሎት አይነቶችን ማብዛት እና ተጨማሪ አጋሮችን ማሳተፍ፤
  • የቴሌብርን ተደራሽነት በማስፋት በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ያሉ ደንበኞች አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት፤
  • ተቋሙ ከሚሰጣቸው ከመደበኛ ቴሌኮም አገልግሎቶት ባሻገር ተጨማሪ የአገልግሎች ዘርፎች ላይ መሰማራት እና የፋይናንስ አቅሙን ማጠናከር፤
  • የውስጥ አሰራሮችን ማዘመን እና የአውቶሜሽን ስራዎችን በማጠናከር ቀልጣፋ አገልግሎት ለደንበኞች መስጠት፤
  • የወጪ ቁጠባ ስራዎችን በማጠናከር የተቋሙን የፋይናንስ ጤናማነት እና ደህንነት ማስቀጠል፤
  • የኩባንያችን አመራር ለፈተና የማይበገር (Resilience) በቢዝነስ ከባቢው ከሚፈጠሩ ሁኔታዎች ጋር በቀላሉ በመላመድ (Adaptive) ተግዳሮቶችን ወደ እድል የመቀየር ሂደቱን አጠናክሮ ማስቀጠል፤
  • የኩባንያችን አመራር እና ሰራተኛን አቅም መገንባትና የቁልፍ አመራርና ባለሙያ የመተካካት ሥርዓት (Succession Planning) መተግበር፤
  • ለማህበረሰቡ በተለያዩ የተቀናጁ መርሃ ግብሮች ድጋፍ በማድረግ የተቋሙን ገጽታና በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን የኔነት ስሜትና ተቀባይነት ማሳደግ፤

2016 በጀት ዓመት ለማከናወን የታቀዱ ዋና ዋና ግቦች

በ2016 በጀት ዓመት የደንበኛ ብዛትን በ8.3% በመጨመር 78 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሲሆን በሞባይል 7.5% በመጨመር 74.74 ሚሊዮን፣ በሞባይል ዳታና ኢንተርኔት በ24% በመጨመር 41.17 ሚሊዮን እንዲሁም የፊክስድ ብሮድባንድ ደንበኛ በ36.3% በመጨመር 842.8 ሺህ በማድረስ አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት መጠንን 71% ለማድረስ ታቅዷል፡፡ የቴሌብር ደንበኞች ቁጥር 28.5% በመጨመር 44.1 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዷል፡፡

ገቢን ከማሳደግ አኳያ ከመደበኛ የቴሌኮም ገቢ ምንጮች በተጨማሪ ሌሎች እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶችን በማካተት የዲጂታል አገልግሎቶችን፣ አዳዲስ እና የተሻሻሉ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አገልግሎቶችን እና የኢንተርፕራይዝ ሶሉሽኖቸን ለገበያ በማቅረብ፤ የቴሌብር ተደራሽነት፣ አገልግሎት አይነቶች እና የአጋሮችን ቁጥር በማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል እንዲሁም የደንበኛ እርካታን፣ ቆይታንና ታማኝነትን በማሳደግ የ2016 በጀት ዓመት አጠቃላይ የገቢ መጠንን 90.5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ የታቀደ ሲሆን ይህም ከዘንድሮው በጀት አመት በ19.4% ዕድገት የሚያስመዘግብ ይሆናል፡፡

በተጨማሪ የደንበኞቻችንን ፍላጎት ለማርካት እና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለንን አጋርነት አጠናክሮ በማስቀጠል፣ የስማርት ስልኮችና ሌሎች የደንበኛ መገልገያ መሳሪያዎች በተለያዩ የክፍያ አማራጮች (installment plan) ለገበያ በማቅረብ፣ በተጨማሪም ለድርጅት ደንበኞች ልዩና ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከመሠረታዊ የቴሌኮም አገልግሎቶች ባሻገር የተለያዩ አስቻይ የሆኑ የዲጂታል ሶሉሽኖችን (Beyond connectivity Solutions) በማቅረብ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በከተማ ማዘመን የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን የማፍጠንና በዚህም አጠቃላይ ሀገራዊ የኢኮኖሚ መነቃቃት እና ተወዳዳሪነት የማሻሻል እንዲሁም ተቋማት ለደንበኞቻቸው የሚሰጡትን አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋና ግልጸኝነት የተሞላበት እንዲሆን ለማስቻል በከፍተኛ ትኩረት ለመስራት ታቅዷል፡፡

የተቋሙ የሰው ኃይል በክህሎት፣ በመልካም ስብዕናና ስነምግባር የተገነባ ብቁ እና ምርታማ እንዲሆን  የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተለይም የኢንዱስትሪውን በፈጣን ሁኔታ ማደግና ተለዋዋጭነትን በሚገባ የሚገነዘብ፣ ከእድገቱ የሚገኙ ትሩፋቶችንና መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ የሚጠቀምና የባለቤትነት ስሜቱ የዳበረ ለማድረግ በትኩረት የሚሰራበት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም  ከኢንዱስትሪው ባህሪ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ፈታኝ ሁኔታዎችንና የውድድር ገበያን በበቂ ዝግጅትና ጥንቃቄ ለመምራት የሚያስችል እውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል መገንባት በስትራቴጂው በግልጽ እንደተመላከተው በዚህ በጀት ዓመትም በትኩረት ለመስራት የታቀደ ሲሆን በተጨማሪም በዘርፉ ከአመራር ቦታዎች ጀምሮ ቁልፍ የባለሙያ ቦታዎች ላይ ተተኪ ለማፍራት (succession planning) እንዲሁም ብቃት ያላቸው የሥራ መሪዎችና ሠራተኞችን በኩባንያው ለማቆየት የሚያስችሉ ሥራዎች በልዩ ትኩረት ለማከናወን በእቅድ ተይዟል፡፡

ኩባንያችን ለነደፈው ስትራቴጂ ተፈጻሚነትና ውጤታማነት በቴሌኮም ቢዝነስ ዘርፍ ከሚሰሩ የኢንዱስትሪው ተዋናይ ባለድርሻ አካላት ጋር በተለይም የቴክኖሎጂ መሳሪያ አቅራቢዎች፣ ከኩባንያችን ምርት አከፋፋይ አጋሮች፣ የይዘት አገልግሎት አቅራቢዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የሚደረግ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ከቢዝነስ አጋሮች ውጭ ወሳኝ ሚና ከሚኖራቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት በሴክተሩ ላይ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችንና ትሩፋቶችን ለሀገራችን የተሻለ ጥቅም የሚሰጡበት ሁኔታ ላይ በመመካከርና በጋራ በመሥራት እንዲሁም ለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በመግባባትና በትብብር መንፈስ መፍትሔ በመፈለግ ላይ ያተከሩ ውይይቶችና የተለያዩ ስምምነቶችን ለማድረግ በእቅድ ተይዟል፡፡

ኩባንያችን ከሚሰጠው የቴሌኮም አገልግሎት በተጨማሪ ለማህበረሰቡ ፋይዳ ያላቸው የማህበራዊ ኃላፊነት (CSR) ጉዳዮች ላይ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ይታወቃል፡፡ በዚህ በጀት ዓመትም በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሰብዓዊ እርዳታና መሰል የበጎ አድራጎት ሥራዎች እንዲሁም ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን አጠናክሮ ለመወጣት አቅዷል፡፡

በመጨረሻም ኩባንያችን ባለፈው በጀት ዓመት ላስመዘገበው የላቀ ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ ደንበኞቻችን፣ የኩባንያችን የስራ አጋሮች፤ ምርትና አገልግሎቶቻችንን አከፋፋይ ወኪሎች፣ አቅራቢዎች፣ ቬንደሮች፣ የሚዲያ አጋሮቻችን እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በሙሉ ልባዊ ምስጋናችን ይድረሳችሁ እያልን ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከኩባንያችን ጋር አብራችሁ እንድትሰሩ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን፡፡

ውድ ደንበኞቻችንና የሥራ አጋሮቻችን ስለአብሮነታችሁ እያመሰገንን፣ ስለደንበኞቹ እርካታ የሚተጋው ኩባንያችን ቀጣዮቹንም አመታት በላቀ አገልግሎት ከእናንተ ጋር በመሆን በተሻለ አገልግሎትና ትጋት አብሮ ለመዝለቅ ተዘጋጅቷል፡፡

ለሁለንተናዊ እድገት የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በጋራ እናፋጥን!

ሐምሌ 20 2015 .

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives